ለብዙዎች አርዓያ የሚኾኑት ፕሮፌሰር!

ፕሮፌሰር ጌትነት ታደለ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህርና ተመራማሪ ናቸው፡፡ ፕሮፌሰሩ በ2008 ዓ.ም በስማቸው የሚጠራ አጠቃላይ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በአዘና ከተማ አስገንብተው ለሕዝብና ለመንግሥት አስረክበው ነበር።

ትምህርት ቤቱ 16 መማሪያ ክፍሎች፣ ቤተ መጻሕፍት፣ ቤተ ሙከራ እና መጸዳጃ ቤት የተሟላለት ነው። አሁን ላይ 780 መደበኛ ተማሪዎችን እና 87 የቅድመ መደበኛ ተማሪዎችን እያስተናገደ ይገኛል። እስከ ስድስተኛ ክፍል እንዲያስተናግድም ታቅዶ የተሠራ ነበር።

አሁን ደግሞ በእሳቸው አስተባባሪነት ከ2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ የማስፋፊያ ግንባታ አሠርተዋል፤ ስምንት ክፍል ያላቸው ሁለት ህንጻዎችን እና ተጨማሪ መጸዳጃ ቤቶችንም በትላንትናው ዕለት አስመርቀዋል። ይህም ት/ቤቱ እስከ 8ኛ ክፍል ድረስ ተማሪዎችን እንዲያስተናግድ ያስችለዋል።

''ሕንጻ መገንባት ብቻውን ትርጉም የለውም፣ ሕንጻውን ተጠቅሞ ራሳቸውን፣ ቤተሰቦቻቸውን እና ሀገራቸውን የሚጠቅሙ ብቁ ዜጎችን መፍጠር ይገባል።'' የፕሮፌሰሩ መልዕክት ነው።

ፕሮፌሰር ጌትነት ታደለ ከዚህ ቀደም ለማህበረሰቡ ምን አስተዋጽኦ አበረከቱ?

- ለዘመናት የሰው ሕይወት ይቀጥፍ እንደነበር የሚነገርለትን የአየሁ ወንዝ ላይ ድልድይ ገንብተው ሕዝባቸውን ታድገዋል።

- ሕዝብና ልዩ ልዩ ድርጅቶችን በማስተባበር በአየሁ ጓጉሳ ወረዳ ከአንደኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን አስገንብተዋል።

- በአንከሻ ጓጉሳ እና በፋግታ ለኮማ ወረዳዎችም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን አስገንብተው ለሕዝብ አስረክበዋል። (አሚኮ)Dr Getnet